ቤኒያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ያለው ውጊያ ማብቂያው ተቃርቧል አሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው ከሃማስ ጋር በጋዛ እያደረገችው ያለው ከፍተኛ ውጊያ ማብቂያው ተቃርቧል ሲሉ ተናገሩ።
ኔታንያሁ ቻናል 14 ለተሰኘው የሀገሪቱ ቴሌቪዥን÷ በራፋህ ያለው ከባድ የጦርነት ምዕራፍ ሊያበቃ እንደሆነና የእስራኤል ጦርም በጋዛ ሰርጥ ያለውን ከባድ የውጊያ ምዕራፍ ለማጠቃለል እንደተቃረበ ገልጸዋል።
ይህ ማለት በጋዛ ሰርጥ ያለው ግጭት ያበቃል ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ከሃማስ ኢላማዎች ጋር የሚደረገው ውጊያ ይቀጥላል ብለዋል።
ኔታንያሁ እስራኤል በሊባኖስ በሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ላይ ጦርነት እንደምትጀምር የሰጠችውን ማስጠንቀቂያ በመጥቀስም÷ በጋዛ ውስጥ ያለው ከባድ የጦርነት ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ጦርነቱ በሰሜኑ ክፍል እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ከፈረንጆቹ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ የእስራኤል እና የሂዝቦላህ ኃይሎች የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማስፈን የሚደረግ ማንኛውም ጥረት የእስራኤልን ፍላጎት ማሟላት አለበት ብለዋል።
በጋዛ ሰርጥ ሃማስ ከስልጣን እንዲወገድ እና በፍልስጤም ግዛት ውስጥ የሚገኙ 100 የሚጠጉ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ብቻ እንደሚስማሙ መግለፃቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።