ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ 3 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር አዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በ2016 በጀት ዓመት በ11 ወራት 3 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለፀ፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከተፈቀደላቸው የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ጋር በሙያዊ አገልግሎት አሰጣጥ እና በታክስ አስተዳደር አሰራር ስርዓት ላይ ውይይት እያደረገ ነው።
በመድረኩ የገቢዎች ሚኒስቴር የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሰለሞን ደርቤ÷ ታክስን በፈቃደኝነት የመክፈል ባህልን በማዳበር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 3 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 3 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 101 ነጥብ 63 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በታክስ ስርዓት ዘርፍ ስልጠና በመስጠት፣ በወቅቱ ኦዲት በማድረግ ፣የደረሰኝ ቁጥጥርና የታክስ ማጭበርበርን በመከላከል የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በታክስ ገቢው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ስርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ቱሉ÷ የተፈቀደላቸው የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች በገቢ አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ በመጥቀስ ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በቅድስት ዘውዱ