በጎንደር ከተማ ከ12 ሰዓት በኋላ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ማሽከርከር ተከለከለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ከዛሬ ጀምሮ የሦስት እግር ተሽከርካሪ ከ12 ሰዓት በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ መንቀሳቀስ እንደማይችል የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ በቡድን በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የሰው እገታ ወንጀል እየጨመረ መጥቷል፡፡
ይህን የማህበረሰቡ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ለመቀነስ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ህጋዊ የከተማ ፈቃድ የሌላቸው አሽከርካሪዎች በተግባሩ እየተሳተፉ መሆኑን በተደረገ ኦፕሬሽን ማረጋገጥ እንደተቻለ የገለፁት ኃላፊው በሁለት ቀን በተደረገ ክትትል 27 ተሽከርካሪዎች ተይዘዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከ12 ሰዓት በኋላ በከተማዋ ሦስት እግር ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የከተማው ማህበረሰብ ቀና ትብብር እንዲያደርግ ተጠይቋል።
የብሎክ አደረጃጀትን በማጠናከር ቤት ለቤት የሚፈፀመውን የስርቆት ወንጀል ለመቀነስ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይገባልም ተብሏል።