Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቀው የዓለም አጭሩ የንግድ በረራ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስኮትላንድ ዌስትሬይ እና ፓፓ ዌስትሬይ መካከል ያለው የአውሮፕላን በረራ አብዛኛውን ጊዜ በአየር ላይ የሚኖረው ቆይታ ከ2 ደቂቃ በታች መሆኑ የዓለምን ክብረ ወሰን እንዲይዝ እንዳስቻለው ተነግሯል።
 
ብዙዎች ለአጭር ጉዞ ወደ መኪና፣ አውቶቡስ ወይም ባቡር መሳፈርን ምርጫቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚገልጸው የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ÷ ነገር ግን በሰሜናዊ ስኮትላንድ ደሴቶች ያለው የተለየ እንደሆነ ያነሳል።
 
የኦርክኒ ደሴቶችን መኖሪያ ያደረጉ ሰዎች ሁለት አማራጮች ብቻ አሏቸው፤ ይህም አዝጋሚ የሆነ የጀልባ ጉዞ በውሃ አካል ላይ ማድረግ ወይም በትንሽ አውሮፕላን አጭር በረራ ማድረግ ናቸው።
 
ምክንያቱም ጀልባው ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ውሃ ምክንያት መስተጓጎል ሊያጋጥመው ስለሚችል ሁለተኛው የቅጽበት በረራ የተሻለው አማራጭ በመሆኑ ተወዳጅና ተፈላጊ ነው፡፡
 
በዌስትሬይ እና በፓፓ ዌስትሬይ ደሴቶች መካከል ያለው በረራ በዓለም ላይ በጣም አጭር የንግድ በረራ ሲሆን÷ ብዙውን ጊዜ የሚቆየው 90 ሰከንድ ብቻ ነው፡፡
 
ነገር ግን አንዳንዴ የአየር ንብረት ሁኔታው ምቹ ሲሆን በረራው ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ዘገባው አመላክቷል፡፡
 
በፈረንጆቹ 1967 የጀመረው ይህ የዓለማችን አጭሩ የንግድ በረራ እስከ አሁን የቀጠለ ሲሆን÷ 2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ የሚሸፍንና ይህም ከአብዛኞቹ ዋና አየር መንገዶች ማኮብኮቢያ ያነሰ እንደሆነ ዘገባው አስነብቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.