Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ የ6ኛው ዙር ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚያስፈጽመውን የ6ኛው ዙር ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚያስፈጽመውን የ6ኛው ዙር ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ቦርዱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የ6ኛው ዙር ቀሪና እና የድጋሚ ምርጫ ድምፅ የመስጠት ሂደትን እንደሚያስፈጽም ይታወቃል።

በዚህም መሠረት በዕለቱ የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ ድምፃቸውን መስጠት እንዲችሉ፣ እንዲሁም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ለማስቻል፣ ቦርዱ የሚከተሉትን ተግባራት ተፈጻሚ እንዲሆኑ “የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የሥነ‐ምግባር ዐዋጅ 1162/ 2011 አንቀጽ 161” ላይ በተደነገገው የመተባበር ግዴታ መሠረት ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ከታች የተዘረዘሩትን ተግባራት ያሳውቃል።

  • ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ አካባቢዎች የሚገኙ የፌዴራልና የክልል መንግሥታዊ ተቋማት ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ. ም. ሥራ ዝግ እንዲያደርጉ፣
  • ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጠት ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ አካባቢዎች የሚገኙ ማንኛቸውም መንግሥታዊ ያልሆኑና የግል ተቋማት በተመሳሳይ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ. ም. ዝግ እንዲያደርጉ፣
  • የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ማለትም ሆስፒታሎችን ጨምሮ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት …ወ. ዘ. ተ) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ ማከናወን የሚችሉ ሲሆን የመተባበር ግዴታው የእነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም።
  • የትራንስፖርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ አካባቢዎች ዜጎች ድምፅ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችንና ዕቅዶችን እንዳይዙ፤

እንዲሁም እንቅስቃሴያቸውን ድምፅ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ ያበረታታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.