በጅግጅጋ የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተገነባው የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
ፋብሪካውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እስኮት ሆክላንደር እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ኡመር ፋሩቅ መርቀው ከፍተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በክልሉ ተወላጅ ወጣት የተገነባው የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካው የተለያዩ የእንስሳት መኖ ምርቶችን በማቀነባበር የሚያመርት መሆኑ ተገልጿል።
አቶ ኡመር ፋሩቅ÷ የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ከሩቅ ቦታ የሚመጣውን የእንስሳት መኖ የሚያስቀር እና ምርቱን በቅርበት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል።
እስኮት ሆክላንደር በበኩላቸው÷ ፋብሪካው ጥራት ያለው የእንስሳት መኖን ለማምረት ከማስቻሉ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የጎላ አስተዋፅዖ ለማበርከት እንደሚያስችል መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡