ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ማዕከል ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቶታል ኢነርጂ ኢትዮጵያ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ማዕከሉን ዛሬ በይፋ አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬቻኡክስ ፣ ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ እና የቶታል ኢነርጂ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ክርስቶፍ ፈራንድ ተገኝተዋል፡፡
ወይዘሮ ሳህረላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የአየር ብክለት ተፅዕኖን ለመቀነስ ቶታል ኢነርጂ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ማዕከል ፋይደው የጎላ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው÷ የማዕከሉ መከፈት ኢትዮጵያ ቅድሚያ የሰጠችውን ለውጥ ለመደገፍ ፈረንሳይ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን ለመቀነስ እያደረገች ላለችው ጥረት ፈረንሳይ ድጋፏን ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
ቻርጅ መሙያ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ብሎም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መሆኑን ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡