የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሚኒስቴር የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ያዘጋጀው ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የመከላከያ ሰራዊት የሥነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጀ እንዳልካቸው ወልደኪዳን፣ የመቻል ስፖርት ክለብ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሰይፉ ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀን፣ የክለቡ አንጋፋ ስፖርተኞች፣ የክለቡ ስፖርተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ክለቡን አስመልክቶ የመነሻ ጽሑፍ የሚቀርብና ውይይት የሚደረግበት መሆኑ ተገልጿል።
ዘንድሮ 80ኛ ዓመት የደፈነው መቻል ስፖርት ክለብ፤ የምስረታ በዓሉን የሚዘክርና የወደፊቱን የክለቡን ጉዞ መሰረት የሚያጸና ‘መቻል ለኢትዮጵያ’ በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱ ይታወቃል።
ከዚህም ውስጥ የገቢ ማስገኛ ቴሌቶን፣ የተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን ማከናወን ከሁነቶቹ መካከል እንደሚገኙበት ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የመርሐ ግብሩ አካል የሆነ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም “መቻል ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል።
የመቻል ስፖርት ክለብ በ1936 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን÷ እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ በልዩ ልዩ ስፖርቶች የተለያዩ ስመጥር ስፖርተኞችን አፍርቷል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ስራ አመራር ቦርድ የክለቡን የቀድሞ ስምና ዝና ለመመለስ የመልሶ ማደራጀት ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።