Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከተቀመጠው አሰራር ውጪ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ ማድረግና የኪራይ ውል ማቋረጥ በጥብቅ የተከለከለ ነው – ቢሮው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአከራይ ተከራይ አዋጅ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ከሕግ ከተቀመጠው አሰራር ውጪ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ ማድረግና የነበረውን የኪራይ ውል ማቋረጥ በጥበቅ የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።

ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማህበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት የቤት ኪራይ ስርዓቱ በሕግ የሚመራ እና ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ተገቢ ሆኖ ስለታመነበት የመኖሪያ ቤት ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 መጋቢት 24/2016 መውጣቱ ይታወቃል።

የከተማ አስተዳደሩም የአዋጁም ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 7/2016 በማውጣት ተግባራዊ ማድረጉን የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም አዋጁ ወጥቶ ተግባራዊ ከሆነበት ቀን ማለትም ከመጋቢት 24 ቀን 2016 ጀምሮ መንግስት ከሚያስቀምጠው የኪራይ ውሳኔ ውጪ በአከራዮች የሚደረግ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡

ስለሆነም አዋጁ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ከሕግ ከተቀመጠው አሰራር ውጪ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ ማድረግና የነበረውን የኪራይ ውል ማቋረጥ በጥበቅ የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል፡፡

ይህ እንዳይፈፀምም ቢሮው ተገቢውን ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርግ እና የሕግ ክልከላውን ተላልፎ የተገኙ አከራዮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስገንዝቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.