በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 17 ሺህ በላይ ጥይት ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በቅንጅት ባደረገው ፍተሻ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 17 ሺህ 350 ጥይት መያዙን አስታወቀ።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አንድ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ጣሂር ሳህሊ እንዳሉት ፥ አፈወርቅ ፀጋዬ የተባለ ተጠርጣሪ መነሻውን ቆቦ ከተማ በማድረግ በሚያሽከረክረው መኪና ውስጥ ለፅንፈኛው የሽብር ተግባር ሊውል የነበር 13 ሺህ የክላሽ ጥይት፣ 2 ሺህ የብሬን ጥይትና አንድ የብሬን ሸንሸል በተሽከርካሪው ላይ በተሰራ ሞደፌክ ተደብቆ ተይዟል።
ወደ ባሕር-ዳር ከተማ ለማድረስ ሲንቀሳቀስ ከመረጃ ደህንነት ጋር የጋራ ክትትል በማድረግ በሮቢት ወረዳ በተጠናከረ የኬላ ፍተሻ ለጥፋት ዓላማ ሊውል የነበረው ጥይት መያዙን ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል አማረ ጌቱ እና እሱባለው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ውስጥ 2 ሺህ 350 የክላሽ ጥይት ይዘው ከቆቦ ወደ ወልዲያ ሲጓዙ በሠራዊቱ መያዛቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡