በሕንድ በተበከለ የአልኮል መጠጥ ምክንያት ብዙዎች ለህልፈት ተዳረጉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡባዊ ሕንድ ታሚል ናዱ ግዛት የተበከለ የአልኮል መጠጥ በመጠጣታቸው ቢያንስ የ34 ሰዎች ህይዎት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
በክስተቱ ለህልፈት ከተዳረጉት በተጨማሪ ከ100 የሚልቁ ሰዎችም በአጣዳፊ ተቅማጥ፣ ትውከት እና ከፍተኛ የሆድ ህመም ለሆስፒታል አልጋ መዳረጋቸውን የመንግስት ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ10 ያላነሱ ባለስልጣናት ከስራ መታገዳቸውም ነው የተሰማው፡፡
ጎቪንዳራዥ የተባሉ የ49 ዓመት የአልኮል ነጋዴ ይህን ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ፥ ሊሸጥ የነበረን 200 ሊትር ከሜታኖል ጋር የተቀላቀለ የአልኮል መጠጥ መያዙን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት በታሚል ናዱ አቅራቢያ በምትገኝ ግዛት በተመሳሳይ በተበከለ የአልኮል መጠጥ ምክንያት ከ12 በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን አስታውሶ የዘገበው ቲአርቲ ዎርልድ ነው፡፡