የ170 አምራች ኢንዱስትሪዎችን የኃይል አቅርቦት ጥያቄ መመለስ መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ባለፉት አስር ወራት የ170 አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሃይል አቅርቦት ጥያቄ መመለስ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የ2016 የአስር ወራት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
በዚህም በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች መሰራታቸው፣ በባለድርሻ ተቋማት ላይ የባለቤትነት ስሜትን የመፍጠር እና ንቅናቄውን ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ ረገድ ውጤት መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር)÷ በየዓመቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚቀርበው የብድር መጠንና የስራ ማስኬጃ የፕሮጀክት ፋይናንስ ድጋፍ ለውጦች እየታዩበት ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት 12 በመቶ የነበረው የብድር አቅርቦት መጠን በ2016 ወደ 16 በመቶ ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት 10 ወራት 710 አዳዳስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ እንደተቻለ መጥቀሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱትሪዎች ሽግግር የተፋጠነ እንደነበር የገለጹት አስተባባሪው÷ ከመሠረተ ልማት አንጻርም የመሬት፣ የኃይልና የትራንስፖርት አቅርቦትን የማሟላት ስራው ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድም በክልል ከተሞች 12 ሺህ ሄክታር መሬት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች መተላለፉን እና ለ170 አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ የሃይል አቅርቦት ጥያቄን ምላሽ መስጠት መቻሉን አንስተዋል፡፡