ከ70 በላይ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ70 በላይ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የተሳተፉበት እና “መሬታችን ለባለሃብቶቻችን“ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የንቅናቄ መድረኩ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተዘጋጀ ሲሆን ለሁለት ወራት የሚቆይ የንቅናቄ መድረክ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም ለማሳደግ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በስታርትአፕ እንዲጀመሩ በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መድረኩ ለሀገር በቀል ኩባንያዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመልክቷል።
በንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ እና የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ከ70 በላይ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ ሀገራዊ የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሰረት በማድረግ የተተገበሩ የሪፎርም ስራዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተሳትፎ አሳድጓል፡፡
በኮርፖሬሽኑ ከተደረጉ የሪፎርም ስራዎች መካከልም የሊዝ ቅድመ-ክፍያ ከ10 በመቶ ወደ 5በመቶ እንዲሁም የሼድ ኪራይ በፊት ከነበረበት 10 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ከ60 በላይ ሀገር በቀል ባለሃብቶች የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው ወደ ስራ መግባታቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡