Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ አድርጓል -የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ንቅናቄ ሀገሪቱ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረጉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ ።

“በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ የዩኒቨርሲቲዎች የላቀ ተሳትፎ ” በሚል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች ፣የዘርፉ ተመራማሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው ።

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ÷ኢትዮጵያን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል ።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ30 ቢሊየን በላይ ችግኞችን የመትከል ፣የማጽደቅና የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል ።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የልማት ዕቅዷ ምሰሶ አድርጋ ወደ ተግባር ከገባች ዓመታት መቆጠራቸውን አስታውሰዋል ።

ይህንን ስርዓት በተለያዩ የዘርፍ ተቋማት የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ለማስረጽ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ወደ ስራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል ።

በተለያዩ የአለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ለሚደረጉ ድርድሮች የሚያስፈልጉ አቅሞችን ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲዎችና ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው አቶ ስዩም ያሳሰቡት።

ለዚህ የሚረዱ የትብብር ማዕቀፎች፣ስልቶች ፣የትምህርት ክፍሎች ፣የስልጠናና ልምድ ልውውጥ ስርዓቶችና ተጨማሪ የጥናትና ምርምር ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ሊገቡ ይገባል ብለዋል ።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.