የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች በትኩረት ይሰራሉ ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የመንግስት የ2016 ዓ.ም የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ላይ ከአገልግሎቱ ሰራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት÷ እድገቱን ለማስቀጠል እየተተገበሩ ያሉ ኢንሼቲቮች በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ አለባቸው፡፡
እድገቱ በሁሉም ዘርፍ ቀጣይነትእንዲኖረው በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ለኢኮኖሚ እድገቱ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ በሁሉም አካባቢዎች በተሻለና በተጠናከረ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የ10 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የፈረንጆቹ 2023-2024 የዓለም አማካይ የኢኮኖሚ እድገት 3 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ በተጠቀሰው ጊዜ 7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ 5ኛ ከዓለም ደግሞ 57ኛ ግዙፉ ኢኮኖሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣዩ ዓመት የሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በ8 ነጥብ 3 በመቶ እንዲያድግ ይሰራልም ብለዋል፡፡
በዚህም ግብርናው 6 ነጥብ 1 በመቶ፣ ኢንዱስትሪው 2 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ 7 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የዋጋ ግሽበቱን አሁን ካለበት 25 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 12 በመቶ ለማውረድ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡