Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በብሪክሱ መድረክ ተባብሮ የመስራት ችሎታዋንና ዓለም አቀፋዊ አጋርነቷን ማስመስከር ችላለች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ የተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም በስኬት ተጠናቋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ 24 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ በማውጣት ለስኬታማነቱ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ የላቀ የዲፕሎማሲ ድል ማስመዝገቧን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገልፀዋል።

(World majority for meltipolar order) ዓለማቀፋዊ ብዝሃነት፣ ለብዝሃ ዋልታ ሥርዓት በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 9 እስከ ሰኔ 12 በተካሄደው ፎረም ጥቂቶች ብቻ የሚወስኑባት ዓለም፣ በብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ስር ለሚገኘው አብዝሃኛው የዓለም ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ ፣ የሀብት ተካፋይነት ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ፍትሃዊ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት ተመክሮበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያም በብልጽግና ፓርቲ በኩል ጠንካራ የአብሮነት አቋሟን አሳውቃለች ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፋዊ የአብሮነት ተግባር ከሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ አሁኑ የተባበሩት መንግስታት በግንባር ቀደም የተሳትፎ ሚና እንደምትታወቅ ፤ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት እስከ አፍሪካ ህብረት እድገት ደረጃም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላት በወርቃማ የታሪክ መዝገብ መፃፉን አቶ አዲሱ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ለተወከሉበት ለብዙሃኑ የዓለም ህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም መከበር በሚደረገው የጋራ ትግል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና በብልጽግና ፓርቲ የተጀመረውን ውጤታማ ተግባር እንዳሳየች አቶ አዲሱ ገልፀዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በመምከር ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ድል በማስመዝገብ ተባብሮ የመስራት ዓለም አቀፋዊ አጋርነቷን ማስመስከር ችላለች ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ ከተመለከቱት ጉዳዮች መካከልም በአፍሪካ ጉዳይ ከአፍሪካ ውጭ ያሉ ሀገራት በፖለቲካ፣ በወታደራዊ ፖለቲካና በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ ሊቆም እንደሚገባ ትኩረታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም በብሪክስ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር የማጠናከሩን አስፈላጊነትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይሄንን ለማሳካት ከብሪክስ አባልና አጋር ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የህዝብ ተቋማት፣ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች የሚሳተፉባቸው የባለ ብዙ ዘርፍ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን አስፈላጊነትም አስቀምጠዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አደም ፋራህ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በተሳተፈበት የብሪክስ እና አጋር ሀገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት ፎረም በርካታ የቀጥታና የጎንዮሽ ውይይቶች ተካሂደውበታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.