ለጤና ጠንቅ የሆነ ህገ ወጥ ጨው አከማችተው የተገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች በገንዘብና በፅኑ እስራት ተቀጡ
የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ነው ዛሬ በነበረው የችሎት ቀጠሮ ተከሳሾቹ በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የወሰነባቸው፡፡
ተከሳሾቹ በጨው ምርትና የማከፋፈል የንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት 1ኛ ታደለ አበባው፣ 2ኛ አቤልነህ ላቀው፣ 3ኛ ሃካን ኮሌንኦግሉ፣ እንዲሁሞ የሚሰሩባቸው ቲቲ አር ኃ/የተ/የግል ድርጅት እና ኤስ ቪኤስ ኃ/የተ/የግል ድርጅቶች ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ህግ እንዲሁም የመድሐኒትና ጤና እንክብካቤ ማቋቋሚያ አዋጅ እና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ማቋቋሚያ አዋጅ ስር የተመላከቱ ድንጋጌዎችን መተላለፋቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተውም÷ተከሳሾቹ የንግድ ፈቃድ አዋጁን በመተላለፍ በሚያዚያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ለሰው ልጅ የጤና ጠንቅ የሆነ የዋጋ ግምቱ 34 ሚሊየን 998 ሺህ 739 ብር ከ20 ሳንቲም የሚገመት በየደረጃው አጠቃላይ 52 ሺህ 128 ኩንታል ህገወጥ ጨው ከአፋር ክልል በማምጣት በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ ገላን ክ/ከ እንዶዴ ወረዳ በተለምዶ ሳሪቲ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ላይ በሚገኙ መጋዘኞች ውስጥ በህገወጥ መንገድ አከማችተው መገኘቱ ተጠቅሷል።
የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት፣ አስረጂ የሰነድ ማስረጃዎች እና የፖሊስ ገላጭ ማስረጃዎች ተያይዞ ከክሱ ጋር ቀርቧል።
በክሱ ላይ ከተጠቀሱ ተከሳሾች መካከል የመጋዘን ሰራተኛ የሆነው 2ኛ ተከሳሽ ብቻ በቁጥጥር ስር ውሎ ክሱ የደረሰው ሲሆን÷ ሌሎቹ በሌሉበት ነው ጉዳያቸው የታየው።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ወንጀሉ መፈጸሙን በማረጋገጥ 2ኛ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ሲሆን÷ ሌሎቹ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።
ይሁንና ሁለተኛ ተከሳሽ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ማስረጃ በተገቢው ማስተባበል ባለመቻሉ በተመሳሳይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
በዚህም ዐቃቤ ህግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ያቀረበ ሲሆን ÷ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ በጠበቃው አማካኝነት የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑንና የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንደሌለበት ገልጾ ሌሎች የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም መርምሮ ዛሬ ረፋድ በዋለው የችሎት ቀጠሮ የገንዘብና የእስራት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።
በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ታደለ አበባው በ3 ዓመት ከ 6 ወራት ጸኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን፣ 2ኛ ተከሳሽ አቤልነህ ላቀው በ 1 ዓመት ከ6 ወራት እስራት፣ 3ኛ ተከሳሽ ሂካን ኮሌንኦግሉ ደግሞ በ 3 ዓመት ከ6 ወራት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
ሌሎቹ ማለትም 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሽ የሆኑት ቲቲ አር ኃ/የተ/የግል ድርጅት እና ኤስ ቪኤስ ኃ/የተ/የግ/ድርጅቶችን ደግሞ እያንዳንዳቸው 100 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከጨው ማምረት ሥራ ለሶሰት ዓመታት እንዲታገዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ