በአማራ ክልል ለተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የተሰጠው ምላሽ የከፋ ችግር እንዳይደርስ አድርጓል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ለተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የተሰጠው ፈጣን ምላሽ የከፋ ችግር እንዳይደርስ ማድረጉን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በ2015/16 በጀት ዓመት ለተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በተሰጠ የሴክተር ተቋማት ምላሽ እና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ በሚሠሩ ተግባራት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የተከሰቱ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ በትኩረት በመሠራቱ የሰውን ሕይወት መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በክረምቱ ወራት የጎርፍ አደጋ፣ የውኃ ወለድ በሽታዎችና ተያያዥ ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ፤ ይህን ባገናዘበ ሁኔታ የመከላከል ሥራዎች፣ የውኃ ማከሚያ እና የመድኃኒት ዝግጅት በማድረግ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡