Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገራት የጀስቲስ ፎረም ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሚመራ ልዑክ ቡድን ሩሲያ በሚካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት የጀስቲስ ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በሩሲያ ሶቺ ከተማ ትናንት መካሄድ የጀመረው ፎረሙ እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

ፎረሙ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የሚመራ ልዑክን ጨምሮ የሩሲያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የቻይና፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሕንድ፣ የግብፅ እና የኢራን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ ነው፡፡

ፎረሙ አባል ሀገራቱ በዓለም አቀፍ ህግ መርህዎችና ደንቦች ላይ የተመሰረተ የብሪክስ ሀገራት የፍትህ ስርዓት እድገትን በተመለከተ የጋራ አመለካከትን እና መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ከመድረኩ ጎን ለጎን አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በሁለትዮሽ የጋራ የምክክር መድረክ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ከኢሪያና ኮንዶዞቫ ጋር በሁለትዮሽ የጋራ ግንኙነት ላይ መወያየታቸውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በዉይይታቸዉም ፥የሩሲያና የኢትዮጵያ ግንኙነትን በፍትህ ዘርፉም ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የእርስ በርስ ጠንካራ ተቋማዊ ትስስር ለመፍጠር በትምህርት፣ በአጫጭር ስልጠናዎች፣ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ስራዎችና አጠቃላይ የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም መርሃ ግብር ተይዟል ነው የተባለው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.