ም/ ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእምነበረድና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእምነበረድና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የማዕድን ሚኒስትር ሐብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) ና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው÷ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ሰላምን በማፅናት ያለውን የማዕድንና የቀርከሃ እምቅ አቅም ለመጠቀም የተጀመረውን ሥራ አድንቀዋል።
በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መኖሩን ተመልክተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ የክልሉን እምቅ አቅም ለልማት በማዋል የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ኃብትና ምቹ የአየር ሁኔታ እንዳለው ጠቅሰው ፥ ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሠረት የሚሆን ንቅናቄ መኖሩንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ÷ በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ግራናይትን ጨምሮ ሰፊ የማዕድን ሀብት መኖሩን ጠቅሰው ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እነዚህ አቅሞችን ወደ ልማት በማዋል ረገድ አበረታች ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያለውን መጠነ ሰፊ የቀርከሃ ሀብትን ጥቅም ላይ ለማዋልም የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡