ጤና ሚኒስቴር እና ግሎባል ፈንድ ከ25 ቢሊየን ብር በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤና ሚኒስቴር እና ግሎባል ፈንድ የቲቪ፣ የኤች አይ ቪ እና የወባ በሽታዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ከ25 ቢሊየን ብር በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመዋል፡፡
ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና በግሎባል ፈንድ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሊንዶን ሞሪሰን ተፈራርመዋል፡፡
ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት ፥ ግሎባል ፈንድ ባለፉት ሁለት አሥርት-ዓመታት የቲቪ፣ የኤች አይ ቪንና የወባ በሽታዎችን ለመቆጣጠርና አጠቃላይ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል የ3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በተከናወኑ የጋራ ጥረቶች ስኬቶች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ፥ ሆኖም ግን አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ ስምምነቱ የቲቪ፣ የኤች አይ ቪ እና የወባ በሽታዎችን ሥርጭት ለመቆጣጠር ለሚከናወነው ሥራ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር ፕሮጀክትን ያካተተ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም የጤና ባለሙያዎችን ከማሰልጠንና የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባሻገር የመድኃኒት አቅርቦትን ለማጠናከር እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት፡፡
በግሎባል ፈንድ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሊንዶን ሞሪሰን በበኩላቸው ፥ በስምምነቱ መሠረት በቀጣይ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ይሆናሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው በትግበራ ሂደቱ ግሎባል ፈንድ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡