Fana: At a Speed of Life!

ብሪክስ ለፍትሐዊ የዓለም የኢኮኖሚና ፋይናንሰ ስርዓት የሚሰራ የትብብር ማዕቀፍ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪክስ ለዓለም ብዙሃን ማህበረሰብ ፍላጎቶች የቆመና ለፍትሐዊ የዓለም የኢኮኖሚና ፋይናንስ ስርዓት የሚሰራ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ የትብብር ማዕቀፍ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

በሩሲያ ቭላዲቮስቶክ እየተካሄደ ያለው የብሪክስ አባልና አጋር አገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፎረም ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑካን ቡድን በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

አቶ አደም ፋራህ የብሪክስና አጋር ሀገራት የፓርቲዎች ፎረም አካል የሆነና “የዓለም ብዙሃንን በሚወክሉ አገራት መካከል የኢኮኖሚና ፋይናንስ ትብብርን በማጎልበት ፍትሐዊ የዓለም ስርዓትን እውን ማድረግ” በሚል ርዕስ በተካሄደ መድረክ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ዓለም እርስ በእርሷ በተሳሰረችበት የአሁኑ ዘመን የኢኮኖሚ ትብብር ምርጫ ብቻ ሳይሆን ለአገራት እጅጉን የሚያስፈልግ የግንኙነት ማጠናከሪያ መንገድ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ከኢኮኖሚ ኢ-ፍትሐዊነት አንስቶ እስከ አየር ንብረት ለውጥና የቴክኖሎጂ እድገት ልዩነቶች ድረስ እየገጠሙን ላሉ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች የጋራ ምላሽ መስጠት አለብን ብለዋል።

ብሪክስ የዓለም ነባር አሰራሮችና ድንበሮችን ተሻግሮ የኢኮኖሚ ትብብር ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም የዓለምን አሁናዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ካስገባው የትብብር ማዕቀፍ ጋር ራሷን ይበልጥ ለማስተሳሰርና የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ፅኑ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል።

የብሪክስ አባል አገራት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ያገለለውና ወደ ጎን የተወው ተለምዷዊ የዓለም የኢኮኖሚ ስርዓት መቀጠል የለበትም በሚል ትግል እንዲደረግ እየተወጡት ያለው ሚና ቁልፍ መሆኑን ነው አቶ አደም የገለጹት።
አባል አገራቱ የሀብቶችና እድሎች ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ስርጭት እንዲመጣ ይበልጥ መሞገት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለችውና 5ኛው የአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልና አጋር አገራት ጋር ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነትን እየፈጠረች እንደምትገኝ ጠቅሰው ይህንኑ የትብብር አድማስ ለማስፋት እንደምትሻም አመልክተዋል።

ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ትምህርት ከትብብር መስኮቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ነው ያነሱት።

ትብብሮቹ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን የልማት ጉዞ ማፋጠን ብቻ ሳይሆን በወዳጅነትና በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።

በፍትሐዊነት፣ በእኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት ጽንሰ ሀሳቦች ላይ የቆመ ፍትሐዊ ዓለም መፍጠር እንደሚያስፈልግ አቶ አደም በገለጻቸው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ጉዳይ ነው።

ለዚህም የብሪክስ አባልና አጋር አገራት ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑበት ልዩ እድል እጃቸው ላይ እንዳለ ገልጸዋል።

ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን እንዲሰፉ በማድረግ፣ ፍትሐዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር በመስራትና ዘላቂ የልማት መርሐ ግብሮችን በመደገፍ የጋራ ብልፅግና የሰፈነባትና እድሎች ለሁሉም ተደራሽ የሆኑባት ዓለም መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል።

የብሪክስ አባልና አጋር አገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፎረም ነገ ይጠናቀቃል መባሉን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመላክቷል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.