Fana: At a Speed of Life!

በኦዲት ግኝት መመለስ ከነበረበት ከ443 ሚሊየን ብር በላይ የተመለሰው 11 በመቶ ብቻ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 92 ተቋማት በኦዲት ግኝት መሰረት ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊየን 23 ሺህ 846 ብር እና 23 ሺህ 55 ዶላር ውስጥ የተመለሰው 48 ሚሊየን 217 ሺህ 965 ብር ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በተቋማቸው የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርቱም 92 መስሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝት መሰረት ተመላሽ እንዲያደርጉ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊየን 23 ሺህ 846 ብር ከ91 ሣንቲም እና 23 ሺህ 55 ዶላር ውስጥ የተመለሰው 48 ሚሊየን 217 ሺህ 965 ብር ከ67 ሣንቲም ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አፈጻፀሙም 11 በመቶ ብቻ ነው መባሉን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በባለበጀት መስሪያ ቤቶች በኩል ርምጃ እስከመውሰድ የሚደርስ መሻሻሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ወ/ሮ መሠረት÷ ነገር ግን ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት ግኝት እና ብር ተመላሽ ያላደረጉ መስሪያ ቤቶች ላይ ምክር ቤቱ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ በበኩሉ በ2014 በጀት ዓመት በዋና ኦዲተር በኦዲት ግኝት መሰረት ብር ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት የተሰጠባቸውና ተመላሽ ያላደረጉ ተቋማት ላይ ተጠያቂነትን እንዲሰፍን አሳስቧል፡፡

ተመላሽ መደረግ ከነበረበት ገንዘብ መካከል ተመላሽ የተደረገው 11 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት÷ ችግሮቹን መመርመር በቀጣይም ገንዘቡን የማስመለስና ተጠያቂነትንም የማረጋገጥ ሥራ መከናወን አለበት ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.