Fana: At a Speed of Life!

ሐሰተኛ የመረጃ ስርጭትን ለመታገል የወቅቱን የሚዲያ ባህሪ መገንዘብ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተስፋፋ ያለውን ሐሰተኛ መረጃ በአግባቡ ለመታገል የወቅቱን የሚዲያ ባህሪ መረዳት እንደሚገባ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከሰኔ 9 እስከ 12 ቀን 2016 በሚካሔደውና “ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር” በሚል መሪ ሐሳብ በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።

“ኃላፊነት የተሞላበት የመረጃ ስርጭት ፍትሐዊ የዓለም ስርዓትን ከመገንባት አንጻር” በሚል ርዕስ በተስተናገደው የፎረሙ ክፍል ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አዲሱ÷ በአሁኑ ወቅት ያልተረጋገጠ የተዛባና ሐሰተኛ መረጃ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በፍጥነት የሚሰራጭበት ሁኔታ እየታየ ነው ብለዋል።

እንደዚህ ዓይነቱን ችግር ለመቋቋም ቴክኒካዊ መፍትሔ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ ባህርያት የመረዳት ባህል ሊዳብር እንደሚገባም በአጽንኦት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህም ለእውነት፣ ለትክክለኛነት፣ ለታማኝነትና ለግልጽነት ቅድሚያ በመስጠት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.