Fana: At a Speed of Life!

ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ በመቅረፅ ሂደት የሚተኮርባቸው ጉዳዮች :-

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እና በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ÷ ግልፅ፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በየፈርጁ ተለይተው ይቀርባሉ፡፡

ከቀረቡ በኋላም ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሆኑ አጀንዳዎች እንደሚቀረጹ የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

በአጀንዳ ቀረፃ ሂደት ውስጥም ኮሚሽኑ የሚከተላቸው ሦስት ዐበይት መርሆች ቀጥለው ቀርበዋል፡፡

1. ለምክክር ጉባዔው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን መመጠን

ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ሲቋቋም በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነት እና አለመግባባት መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ኮሚሽኑ የተቋቋመው ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚረዱ ብሎም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲመነጩ ሁነኛ ሚናን ለመጫወት እንጂ÷ በአንዳንድ መድረኮች እንደሚስተዋለው ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ችግሮች መፍታት የሚችል ተደርጎ መወሰዱ ብሎም ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ የሚነሱ ጉዳዮችን እንደሚያስተናግድ መጠበቁ ሊስተካከል የሚገባው ዕይታ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው የሚገቡ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ወደ ምክክር ጉባዔው እንዲቀርቡ የሚያደርገውም በዚሁ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

2. ድምፃቸው ጎልቶ የማይሰማ የማሕበረሰብ ክፍሎች አጀንዳዎች በአግባቡ መካተታቸውን ማረጋገጥ

ኮሚሽኑ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን መሰረት አድርጎ ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡትን ሲቀርፅ ድምፃቸው ጎልቶ የማይሰማ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ድምፅ ማንፀባረቅ መቻሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

3. ወቅታዊና እጅግ አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት

ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የሚሰበስባቸው ቀጥሎም የሚቀርፃቸው አጀንዳዎች በቁጥር ብዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢገመትም÷ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ እና አፋጣኝ መፍትሔን የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ያቀርባል፡፡

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.