የዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 60 በመቶውን ለመሸፈን ተስማሙ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከሚያስፈልጋት 10 ቢሊየን ዶላር ውስጥ ከግማሽ በላዩን ለመሸፈን ተስማሙ።
ኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው እና የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ያለችውን ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በቅርቡ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፉን ማሻሻል፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠርና የእዳ ጫናን መቀነስ እንዲሁም የወጪ እና ገቢ ንግዱን ሚዛን ማስጠበቅን የትኩረት አቅጣጫው አድርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ከማሻሻያ ስራዎቹ ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት፥ የፋይናንስ ስርአቱ የነበሩበትን ችግሮች ለማስተካከል የገንዘብ ፖሊሲው መሻሻሉን ተናግረዋል።
የገቢ አሰባሰቡም ለውጥ እየታየበት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው ኢኮኖሚው ማመንጨት የሚችለውን ገቢ በመሰብሰብ የግብር ገቢ ከሀገራዊ ምርት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት።
ለአብነትም የቁርጥ ግብር መስተካከሉን ጠቅሰው የቅንጦት እቃዎች ላይ የሚጣለው ቀረጥ (ኤክሳይስ ታክስ) ማሻሻያ ተደርጎበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚፀድቅ አንስተዋል።
በስኳር፣ ቴሌኮም፣ ሃይል ዘርፍ፣ ባቡር፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሎጂስቲክ ዘርፎች የተጀመረው የፕራይቬታይዜሽን ስራም መቀጠሉን ገልጸዋል።
የማምረቻ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፎችን ለማነቃቃት ስራ እየተሰራ ሲሆን፥ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአሊባባ ጋር ከተደረሰው ስምምነት ባሻገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን የሚያቀላጥፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለእነዚህና በአጠቃላይ ለሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ 10 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) 60 በመቶውን ለመሸፈን መስማማታቸውን ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።
አያይዘውም ቀሪውን ገንዘብ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በፋሲካው ታደሰ