Fana: At a Speed of Life!

ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች – አምባሳደር ጃንግ ካንግ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ጃንግ ካንግ ተናገሩ።

አምባሳደሩ ÷ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በተለያዩ የትብብር መስኮች ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፣ በምጣኔ ኃብትና በልማት ዘርፎች ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በሌሎች የትብብር ዘርፎችም እየሰፋ መምጣቱንም ነው ያነሱት።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሪያ ሪፐብሊክ የነበራቸው ጉብኝትም እያደገ የመጣውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

በይፋዊ የሥራ ጉብኝቱ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በኢትዮጵያ ፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንና በደቡብ ኮሪያ ፀረ-ሙስናና ሲቪል መብቶች ኮሚሽን መካከል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በቀጣይ አራት ዓመታት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የ1 ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ማዕቀፍ ሥምምነትም ተፈራርመዋል፤ ይህም ሥምምነት የሀገራቱን ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም ሁለቱ ሀገራት የደረሱት የፋይናንስ ትብብር የድጋፍ ሥምምነት ኢትዮጵያ የተሻለ ምጣኔ ኃብትን በመገንባት ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ እያከናወነች ላለው ተግባር አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለሥምምነቶቹ ተግባራዊነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.