በክልሉ የዜጎችን የማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚነት ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎትን በተቀናጀ አሠራር በማሳለጥ የተጋላጭ ዜጎችን ተጠቃሚነት ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ።
በክልሉ የማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚስችል የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ተመስርቷል።
ምክር ቤቱ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን አቀናጅቶ የመሥራት፣ ጅምሮችን ከተሟላ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ጋር በማቀናጀት ውጤታማ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።
ፖሊሲው የልማታዊ ሴፍቲኔትና የማኅበራዊ መድንን ማስፋፋት፣ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች የሕግ ጥበቃና ድጋፍ መስጠትና የመሰረታዊ አገልግሎቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ላይ እንደሚያተኩር ተመላክቷል፡፡
እስካሁን ሲሰጡ የቆዩ የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎች በግለሰቦችና በተቋማት በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረቱ ሲሆን÷ ምክር ቤቱ አደረጃጀቱን እስከ ታችኛው መዋቅር በማውረድ ሥራውን ለመምራት ያስችላል ተብሏል።
የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንዳሉት÷ምክር ቤቱ ለማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚውል ሃብትን ማደራጀት፣ ማስተዳደርና የራስን ማኅበራዊ ችግሮች በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ጉልበት ይፈጥራል፡፡
ስለሆነም ም/ቤቱ የማኅበራዊ ዘርፉ የልማት ፕሮግራሞችን የማቀናጀትና የማስተሳሰር ሥራ ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ