የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና የፍትሕ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ ጥላሁን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ ከጠንካራ መንግስት መገለጫዎች መካከል ዋነኛው በህብረተሰቡ ቅቡልነት ያለው ጠንካራ የፍትሕ ተቋማትና ሥርዓት መኖር ነው ብለዋል።
የፍትሕ ተቋማትን በማጠናከር በህብረተሰቡ ቁብልነት ያለው የፍትሕ ተቋማትና ይበልጥ ተአማኒነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በመተግበር ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ይህንንም ከግብ ለማድረስ በክልሉ ምክር ቤት ሃላፊነት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ነው የተናገሩት።
ፍትሕ ሲረጋገጥ ጠንካራ መንግስት ይኖራል፤ ህብረተሰቡም በመንግስት ላይ ይበልጥ ጽኑ እምነት ያሳድራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የልማት ሥራዎችን በመስራት ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው ጠንካራ የፍትሕ ተቋማትን በመገንባት ፍትሕን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡