አፍሪካና ላቲን አሜሪካ ድምጻቸው እንዲሰማ በዓለም አቀፍ ተቋማት የተሻለ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካና ላቲን አሜሪካ ድምጻቸው እንዲሰማ በዓለም አቀፍ ተቋማት የተሻለ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከሰኔ 9 እስከ 12 ቀን2016 በሚካሔደውና “ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር” በሚል መሪ ሃሳብ በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በፎረም ላይ አቶ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር፥ አፍሪካና ላቲን አሜሪካ ድምጻቸው እንዲሰማ በዓለም አቀፍ ተቋማት የተሻለ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ብሪክስ አዲስ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡
ፓርቲያችን ብሪክስ በዓለም አቀፍ መድረክ ያለውን አቅም ይገነዘባል ያሉት አቶ አደም፥ ይህም ፓርቲው ብሪክስ እየሰራ ያለውን እንደሚከተልም ነው የገለጹት፡፡
በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረምም የበለጠ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ለኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማደግ አስተዋፅዖ የሚያበረክት የፋይናንስና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ለመለወጥ ያለውን ዝግጁነትንም አጽንዖት በመስጠት መግለጻቸውን ከዩናይትድ ራሺያ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡