እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ዕርዳታ እንዲገባ በሚል ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ገታች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ዋና መንገድ ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲገባ ወደፊት ገደቡ መነሳቱ እስከሚገለጽ ድረስ በየቀኑ ለተወሰኑ ሠዓታት ወታደራዊ እንቅስቃሴውን መግታቱን አስታወቀ፡፡
እንደ ጦሩ ገለጻ÷ ከኬረም- ሻሎም ማቋረጫ ወደ ሳላህ አል-ዲን እና ወደ ሰሜን በሚወስደው መንገድ ወታደራዊ እንቅስቃሴው ከትናንት ጀምሮ በየቀኑ ለሠዓታት ጋብ ይላል፤ ይህም ወደፊት እስከሚገለጽ ድረስ ይቀጥላል፡፡
በአንጻሩ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ የሃማስ ታጣቂዎችን ያነጣጠረው ውጊያ ይቀጥላል ማለቱን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ለማስቆም ከፍ እያለ ከመጣው ዓለም አቀፍ የተኩስ አቁም ግፊት ባሻገር የሚቀርቡ የተኩስ አቁም ስምምነቶች አሁንም ፍሬያማ አለመሆናቸው ሬውተርስ ዘግቧል።