Fana: At a Speed of Life!

የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የንግዱን ዘርፍ ያሳልጣል- ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የንግድ እና ቱሪዝም መስኩን በይበልጥ ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት የፌደራል፣ የኦሮሚያ ክልል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም÷ የአውሮፕላን ማረፊያው ተገንብቶ አገልግሎት መጀመር በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ጸጋ በተሻለ ለማልማት እና የአካባቢውን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማስፋት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም አካባቢው ያለውን የቱሪዝም ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል፣ የሕዝቦችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለማቀላጠፍ ብሎም በአጠቃላይ የሕዝቡን ሕይወት ለመቀየር ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ በሣምንት ሦስት ጊዜ እንደሚበር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.