የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ በዓሉ በመካ እና መዲና ለዒድ ሰላት ከሀገሪቱና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በመጡ የእስልምና እምነት ተከታዮች በተገኙበት እየተከበረ ነው፡፡
በዚህም ምእመኑ (ሃጃጆች) የሃይማኖታዊ ሥርዓቱ አካል የሆነውን ጠጠር የመጣል ተግባርና ሌሎች ሥርዓቶችን ከመግሪብና ከኢሻ ሰላት በኋላ እንደሚያከናውኑ ተገልጿል፡፡
ለዚህ ሥነ-ስርዓትም በሙዝዳሊፋህ ምሽቱን ማሳለፋቸው ነው የተገለጸው፡፡
በተመሳሳይ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች፣ ቱርክ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ዮርዳኖስ፣ ፍልስጤም፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ሊቢያና ግብጽ በዓሉን በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች እያከበሩ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ የአሜሪካ አካባቢዎች፣ በብሪታኒያ፣ በአውሮፓ እና በካናዳ በዓሉ ነገ እንደሚከበር ተጠቁሟል፡፡
የዘንድሮው ዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል አከባበር ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ አጅ ቴሌቪዥን ነው የዘገበው፡፡