Fana: At a Speed of Life!

የሀገራችን ሙስሊም ማኅበረሰብ የመደጋገፍ ባህል ከተረጂነት ለመላቀቅ ወሳኝ ዕሴት ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በሙስሊም ማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለው በዓል ነው ብለዋል።

ዐቅሙ እና ሁኔታው የፈቀደላቸው ምዕመናን የሐጅ ሥነ ሥርዓትን በመፈጸም ያከብሩታል በማለት ገልጸው፤ ሌሎች ደግሞ በየሀገራቸው በጋራ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በጸሎት፣ በመደጋገፍና በአብሮነት እንደሚያከብሩት ጠቅሰዋል።

በሀገራችንም ሙስሊሞች በዓሉን በጸሎት፣ ማዕድን በማጋራት እንዲሁም በደስታ በፍቅር ተጋግዘው ሲያሳልፉ እየያን አድገናል፤ አብረንም አክብረናል ብለዋል።

የዘንድሮ በዓል ሲከበር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመጠየቅ እና በመደገፍ እንዲሁም ዐቅመ ደካሞችን በመንከባከብ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ የሀገራችን ሙስሊም ማኅበረሰብ የመደጋገፍ ባህል ከተረጂነት ለመላቀቅ ለምናደርገው ትግል ወሳኝ ዕሴት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

እርስ በእርሳችን በመደጋገፍ በተረጂነት ከመታወቅ መውጣት አለብን ያሉት አቶ ተመስገን፤ ለዚህ ደግሞ በበዓል ጊዜ የምናደርገውን መደጋገፍ የዘወትር ተግባር ማድረግ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

እንደ ሀገር ላለፍንባቸው ችግሮቻችን መፍትሔ የሆነው የሽግግር ፍትሕ እና መፃዒ አብሮነታችንን ለማጎልበት ወሳኝ ለሆነው የሀገራዊ የምክክር ውጤታማነት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የበኩሉን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.