የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ለዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል አደረሳችሁ አደረሰን ሲሉ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በዓሉን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአረፋ በዓል ሲነሳ ስለመንፈሳዊ መደማማጥና ሞራላዊ ስብዕና፣ በጎነትንና ተካፍሎ የመብላትን ስብዕና ስለመላበስ የሚያመላክቱ አስተምህሮቶች አብረው ይነሳሉ ብለዋል።
የአረፋ በዓል በክልሉ ተወላጅ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ተራርቀዉ የቆዩ ቤተሰቦች በአካል ተገናኝተዉ የሚጠያየቁበት፣ መንፈሳቸዉን የሚያነቃቁበት የርስበርስ ግንኙነትን ማደሻ ማህበራዊ እሴትም ጭምር ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና ለተቸገሩ ወገኖች የመድረስን ልምድ ለማጠናከር የአረፋ በዓል የፈጠረዉን ምቹ ዕድል ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በማገዝና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ እንዲያሳልፍ ጥሪ አቀረቡ።
በዓሉ በፍቅር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት እንዲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ አንድነቱንና ወንድማማችነቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የአረፋ በዓል ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ መሆን እንደሚኖርበትም ማመልከታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
እንዲሁም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢድ አል-አድሀ (አረፋ) በዓል በኃይማኖታዊ ይዘቱም የመታዘዝ፣ የመስዋዕትነት፣ ያለመጠራጠር፣ የእምነት ፅናት ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የእስልምና እምነት አስተምህሮ ሰላምን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን የሚሰብክ ነው ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ፤ በዜጎች መካከል አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ይቅር ባይነትን የማጎልበት ድርሻው ላቅ ያለ መሆኑም አስታውቀዋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ እምነቱ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ካለው ለሌላቸው በማካፈል በዓሉን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡