ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በ25 ከተሞች የተካሄዱ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ስኬታማ ነበሩ – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ በ25 ከተሞች የተካሄዱ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ስኬታማ ነበሩ ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ አስታወቁ።
የተካሄዱትን የህዝብ ውይይት መድረኮች አፈፃፀም መድረኮቹን ከመሩት ከፍተኛ አመራሮች ጋር አፈጻጸሙ መገምገሙን ገልጸዋል።
አቶ አደም ፋራህ ጉዳዩን በተመለከተ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:¬-
ከተረጅነት አስተሳሰብ መላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን በተመለከተ በ25 የሀገራችን ትላልቅ ከተሞች የተካሄዱትን የህዝብ ውይይት መድረኮች አፈፃፀም መድረኮቹን ከመሩት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ገምግመናል። ለአመራሩ የልማት ሥራዎች ጉብኝትና ለሕዝብ ውይይት መድረኮቹ ስኬት ብቁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመሰራታቸው የተያዘው እቅድ በውጤታመነት መፈፀሙን አረጋግጠናል።
በየከተማው ሕዝቡን ለማወያየት የሄዱት የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በከተሞቹና አከባቢያቸው የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በየአከባቢው የብልፅግና ፓርቲ እሳቤዎችና እቅዶች መሬት ወርደው በተጨባጭ ውጤት እያመጡና የሕዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለቀጣይ ክትትልና ድጋፍ የሚሆን ግብዓትም አግኝተዋል። ለሚመሩት ክልል/ከተማ ስተዳደር ተሞክሮ የሚሆኑ ልምዶችንም ቀስመዋል።
በሕዝብ ውይይት መድረኮቹ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ከ32ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች መሳተፋቸውን አረጋግጠናል። ከተሳታፊዎች ጋርም በአጀንዳው ላይ የተሟላ መግባባት መፍጠር ተችሏል።
በውይይቱ ሕዝቡ ተረጅነት እና ልመና ከህዝባችን ባህልና እሴት ጋር በፍፁም የማይሄድ ክብረ-ነክ ተግባር በመሆኑ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት በዚህ ደረጃ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ ሕዝብ እንዲወያይበት ማድረጉ እጅግ የሚያስመሰግን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው እንደ ሀገር ሰርተን መለወጥ የምንችልበት በቂ ፀጋ እያለን ጠንክረን ባለመስራታችን አዋራጅ ለሆነው ልመናና ተረጅነት ስለተጋልጥን በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል ብለዋል።
በመሆኑም በየአከባቢያችን የሚገኙ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የስራ ባህል ለውጥ በማምጣት ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂ ዜጎችን ብሎም ሀገራችንን ከልመናና ተረጂነት ለማላቀቅ እንደሚረባረቡ ቃል ገብተዋል።
የመድረኮቹ ተሳታፊዎች በእድሜ፣ በአካል ጉዳት ወይም በሌላ የጤና ችግር ምክንያት መስራትና የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ የማይችሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችል የቆየ ባህል አለን፣ ይህንን መልካም ባህል ስርዓታዊ ማድረግ ከተቻለና መንግስትም የድርሻውን ከተወጣ የሚቸገር ዜጋ አይኖርም ብለዋል።
በመሆኑም ትናንት አባት፣ እናት፣ አያቶቻችን በደማቸውና በአጥንታቸው ነፃ ሀገር አስረክበውናል። ከተረጂነትና ልመና ለመላቀቅ የጀመርነው ጥረት ደግሞ የዛሬው ትውልድ የኢኮኖሚ ነፃነቷን አረጋግጣ የተሟላ ሉዓላዊነት የተጎናፀፈች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግበትን ሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ የሚያሳካበት ወሳኝ ተግባር በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።