Fana: At a Speed of Life!

የጉህዴንና ቤህኔን አመራሮችና ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቀሪ የጉህዴን እና የቤህኔን አመራሮች እና ታጣቂዎች ጋር መግባባት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ ባለፉት ዓመታት መንግስት በክልሉ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጣቂዎች ጋር ባደረገው የሰላም ስምምነት በክልሉ ሰላም መስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ቀሪ የጉህዴን እና የቤህኔን አመራሮች እና ታጣቂዎች መኖራቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት፡፡

አሁን ግን ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሠላም ጥሪን በመቀበል በሰላማዊ መንገድ በመታገል ለዜጎች ሠላም እና ደህንነት ሲባል ከረጅም ጊዜ ውይይት በኋላ መግባባት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

መንግስት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የግጭት መንስኤ የሆኑትን አጀንዳዎች በማስቀረት የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማስቀጠል በርካታ ተግባራት ማከናወኑን አውስተዋል።

የክልሉ ህዝብ የሚናፍቀውና የሚያስፈልገው ጫካ ገብቶ መሳሪያ መማዘዝ ሳይሆን የዘላቂ ሰላም እና ልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሆነ አብራርተዋል።

አሁንም ጫካ የቀሩ አመራሮች እና ታጣቂዎች ካሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ የክልሉ መንግስት በደስታ እንደሚቀበል መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የታጣቂ አመራሮች በበኩላቸው÷ አሁን በክልሉ የተገኘውን ሰላም በመጠቀም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ስኬታማነት ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ታጣቂዎች ወደ መንግስት በመቅረብ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን አቶ አሻዲሊ አመስግነዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.