Fana: At a Speed of Life!

በአኝዋሃ ዞን ያለውን የተፈጥሮ ደን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስችል ረቂቅ ጥናት ለክልሉ ካቢኔ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በአኝዋሃ ዞን ያለውን የተፈጥሮ ደን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ባዮስፌር ሪዘርቭነት ለማስመዝገብ የሚያስችል ረቂቅ ጥናትን በተመለከተ የክልሉ ካቢኔ አባላት ተወያይተው ውሳኔ አሳልፈዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷ ይህንን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በዩኔስኮ በባዮስፌር ሪዘርቭነት ለማስመዝገብ ጥናት መጠናቀቁ ያስደስታል ብለዋል።

የሰው ልጅ አኗኗር ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የተፈጥሮ ሃብቱን በመጠበቅና በመንከባከቡ ረገድ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት የተፈጥሮ ደኑ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

አካባቢው ከ1 ሺህ የሚበልጡ የእፅዋትና የተለያዩ እንስሳት ዝርያዎችን በውስጡ አምቆ የያዘ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑ በሪፖርቱ መቅረቡ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያስረዳል፡፡

ጥናቱ የተካሄደው ”መልካ ኢትዮጵያ” በተባለ ሀገር በቀል ድርጅት ከአኝዋሃ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር ሲሆን÷ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የማጃንግ የተፈጥሮ ደንን በማጥናት በባዮስፌር ሪዘርቭነት እንዲመዘገብ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.