Fana: At a Speed of Life!

የወባ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም ባለድርሻዎች በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ያለውን የወባ ስርጭት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላከተ።

የወባ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ያለመ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በሚዛን አማን እየተካሄደ ነው።

የሀገሪቱ አብዛኛው አካባቢ ለወባ ስርጭት አመቺ በመሆኑ 69 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተናግረዋል።

ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ከፍተኛ ስርጭት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ሀገር 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ገልጸው፤ ይህንን ስርጭት 50 በመቶ ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በክልሉ የወባ ስረጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹ ሲሆን በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የስርጭቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያት የጤና ተቋማት ደረጃ ተመጣጣኝ አለመሆን እና የህክምና መሳሪያዎች ብልሽትን እንደ ምክንያትነት ጠቅሰው፤ ይህን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተስፋፋውን የወባ በሽታ ለመግታት እና በታሰበው ልክ 50 በመቶ መቀነስ እንዲቻል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል።

በፍሬው ዓለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.