Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያላትን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ እቅድ ማስፈጸሚያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።

የባህልና ስፖርት ዘርፍ አፈጻጸምን በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት አቶ ቀጄላ መርዳሳ÷ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታስተናግድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችና ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ዋንጫን በማስተናገድ ያላት ልምድ መካተቱንም ተናግረዋል።

በዋጋ ማስተካከያ ምክንያት ዘግይቶ የነበረው የብሔራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ ስታዲየም) ችግሩ ተፈቶ አዲስ ተቋራጭ ቀሪውን የስታዲየም ግንባታ ስራ የካፍ መመዘኛን ባሟላ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።

የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምና ሌሎች ስታዲየሞችም የካፍ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ የመገንባት ስራ በፍጥነት እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል መንግስት ፌዴሬሽኖችና ማህበራቶች ከበጀት ድጎማ ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በባህል መስክ የኢትዮጵያን ታሪኮችና ባህሎች አቅፎ የያዘ የባህል ማዕከል ግንባታ እንደሚከናወን ለዚህም የዲዛይን ዝግጅት ስራ መጠናቀቁንና ማዕከሉን ለመገንባት የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መወሰዱን አብራርተዋል።

ሚኒስቴሩ ተቋማዊ አቅሙን ለማጎልበት እያደረጋቸው ያሉ ማሻሻያዎች፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እያከናወኗቸው የሚገኙ ስራዎችና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች መገምገማቸውንም አክለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.