Fana: At a Speed of Life!

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰሩ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመደገፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም ዘር በማቅረብ፣ የውሃ ሞተርና ሸራ በነፃ በማከፋፈል እንዲሁም በገጠር ቀበሌዎች ላይ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማጎልበት እየተደረጉ የሚገኙ ድጋፎች ለአብነት ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለከተማው ማህበረሰብ እንዲያቀርብ በማድረግም የገበያ ትስስርን ከመፍጠር ባለፈ የከተማው ማህበረሰብ የኑሮ ውድነት ችግርን ለማቃለል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተከናወኑ ሥራዎችም ቀድሞ ከነበረውን የዋጋ ንረት አንፃር መሻሻሎች መታየታቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለፁት።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ ተስፋ ሰጪ አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው÷በዚህም በዋናነት የወተት፣ የዶሮ፣ የእንቁላል እና የማር ምርቶችን የማስፋት ሥራዎች ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል።

በቀጣይም ለአርሶ አደሩ የሚደረጉ ድጋፎችን በማጠናከር የሌማት ትሩፋት ሥራዎች የበለጠ በማጎልበት ምርታማነት እንዲያድግና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በቁርጠኝነት ይሰራል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.