የቡድን 7 ሀገራት የሩሲያ ንብረቶችን በዋስትና በመያዝ 50 ቢሊየን ዶላር ብድር ለዩክሬን ፈቀዱ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡድን 7 ሀገራት የተያዙ የሩሲያ ንብረቶችን በዋስትና በመጠቀም 50 ቢሊየን ዶላር ብድር ለዩክሬን እንዲሰጥ ተስማምተዋል፡፡
የቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች በሐማስ እና እስራኤል እንዲሁም በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ላይ በጣልያን እየመከሩ ነው፡፡
ዛሬ የጀመረው ስበሰባው ለሦስት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ፥ መሪዎቹ በዛሬው ውይይታቸው በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ ተወያይተዋል፡፡
በዚህም የተያዙ የሩሲያ ንብረቶችን በዋስትና በመጠቀም ለዩክሬን የ50 ቢሊየን ዶላር ብድር እንዲሰጥ የቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተዋል፡፡
ይህን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎች ይፋ እንዳልተደረጉና ዝርዝሩ ላይ አሁንም እየመከሩበት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ይሁን እንጂ የሩሲያ ንብረቶችን በዋስትና መጠቀምን በተመለከተ አሜሪካና አውሮፓውያንን ያፋጠጠ ጉዳይ መከሰቱ ተመላክቷል፡፡
ይህም የተያዙ የሩሲያ ንብረቶች ብድሩን ለመደገፍ በቂ ካልሆኑ ሃላፊነቱን ማን ይወስዳል የሚል ነው፡፡
በዚህም አንዳንድ የአውሮፓ ባለስልጣናት አሜሪካ ምስጋናውን ወስዳ ሃላፊነትና ችግሩን ለአውሮፓ ህብረት እያሸከመች ነው ሲሉ መውቀሳቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡
300 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡት አብዛኛዎቹ የተያዙ ንብረቶች በአውሮፓ ህብረት ውስጥ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ፥ ሞስኮ ንብረቶቿን ለመውሰድ የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ ስርቆት እንደሆነ ደጋግማ አስታውቃለች፡፡
ለዚህም ተመጣጣይ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች ነው የተባለው፡፡