Fana: At a Speed of Life!

የአየር ሃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር ከተቋሙ ደህንነት አልፎ የአካባቢውን ሰላም እያረጋገጠ ይገኛል – ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ሃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር ከተቋሙ ደህንነት አልፎ የአካባቢውን ሰላም እያረጋገጠ እንደሚገኝ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ የጥበቃ ክፍለ ጦሩ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ እንዳሉት÷ራሱን፣ ተቋሙንና ሀገሩን የሚጠቅም እንዲሁም የተሰጠውን ግዳጅ በአግባቡ መወጣት የሚችል ጠንካራ ሃይል ወሳኝ ነው፡፡

ሰራዊቱም ይህን ተልዕኮ በመገንዘብ ፍፁም በሆነ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና በሀገር ፍቅር ስሜት ተልዕኮውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

የአየር ሃይል የሠራዊት ስነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ በበኩላቸው÷ መድረኩ ሠራዊቱ እስከ ዛሬ ድራስ የፈፀማቸውን ገድሎችና እያጋጠማቸው ያለውን ተግዳሮቶች መፈተሽ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

የአየር ሃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ወንዱ ወልዴ÷የጥበቃ ክፍለ ጦሩ ከተቋሙ አልፎ ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ በመስራት ሰላምን ለማረጋገጥ አበረታች ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

የጥበቃ ክፍለ ጦሩ አባላት ተቋሙንና አካባቢውን ከመጠበቅ ባሻገር አየር ሃይሉ የያዘውን የለውጥ ጎዳና ተከትሎ የሚሰራ ማንኛውንም የልማት ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ይህንን ውጤታማ ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.