2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አስር ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
የ2016 በጀት ዓመት የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ዘርፉ በ10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት መጨመሩን ገልጸው፥ ይህም የ7 ነጥብ 9 በመቶ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከታታይ የተተገበረው ”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።
በዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ባለፉት አስር ወራት129 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው ያብራሩት።
በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ እንዲገቡ እና የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ መደረጉን አንስተዋል።
በተጨማሪም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የፋብሪካ ምርቶችን ለመተካት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሁነኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው÷ባለፉት 10 ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡