አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የአገልግሎት አሠጣጥ ዘርፉን ለማሻሻልና ለማዘመን የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ ገልፀዋል።
ለምክር ቤቱ አባላት የመንግስትን አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲን ለማስፈፀም በተዘጋጀው ረቂቅ የፌዴራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ መንግስት የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን ለማድረግ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መጠነ ሠፊ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አፈ ጉባዔዋ አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ወደ መረጣቸው የህብረተሰብ ክፍል በሄዱበት ወቅት÷ የሰላምና ጸጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የመልካም አስተዳደር መጓደል እንዲሁም በመሠረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ ጥያቄዎች መነሳታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም መንግስት ጥያቄዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ዙሪያ ከሲቪል ሰርቪስ በመጡ የስራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ከተወካዮች ምክርቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።