Fana: At a Speed of Life!

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ የሥነ-ስርዓትና ፍሬ ነገር ሕጎች እየተዘጋጁ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለመተግበር በአዋጁ የተጠቀሱ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ የሥነ-ስርዓትና ፍሬ ነገር ሕጎች እየተዘጋጁ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን÷ በዚህም የፍትሕ ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱ የመጨረሻዎቹ 100 ቀናት የሕግና ፍትሕ ሥርዓቱ ያለበት አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡

በግምገማውም የሽግግር ፍትሕ መጽደቅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን የገለጹት ጌዲዮን (ዶ/ር)÷ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ጥናቶች፣ ምክክሮችና የባለድርሻ አካላትን የነቃ ተሳትፎ አካቶ መጽደቁን አስረድተዋል፡፡

ፖሊሲውን ለመተግበር የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ መውጣቱን ጠቅሰው÷ በፖሊሲው የተመላከቱ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ የሥነ-ስርዓትና ፍሬ ነገር ሕጎች እየተዘጋጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የፍትሕ ዘርፉን ለማሻሻል በፌደራልና በክልል ደረጃ ገቢራዊ የሚደረጉ ሀገር አቀፍ ሕጎችና አሰራሮች መውጣታቸውንም ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአስተዳደር ሥነ-ስርዓት አዋጅን ማስተግበር፣ የወንጀል ሥነ-ስርዓት አጽድቆ ገቢራዊ ማድረግ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የማሕበረሰብ ተኮር የፍትሕ አገልግሎት ወይም ባህላዊ ፍርድ ቤትን የተመለከተ ሞዴል ሕግ ተዘጋጅቶ ለክልሎች መላኩንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የፍትሕ ስርዓቱን በማሻሻል የዜጎችን ተጠቃሚነት ማጎልበት የሚችሉ ማሕበረሰብ ተኮር የፍትሕ አገልግሎት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

የአሥተዳደር ሥነ-ስርዓት አዋጅን በሁሉም ክልሎች ገቢራዊ ማድረግ እና የወንጀል ፍትሕ ስርዓቱን ማሻሻል የቀጣይ የትኩረት መስክ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.