ኢትዮጵያና ሞሮኮ በሰላም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሞሮኮ በሰላም ግንባታ ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ነዛሃ አላኦኢ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው÷ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት እና መሰረታዊ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሥራዎች እንዲጠናከሩ ለማድረግ የሚያከናውነውን ተግባር በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያና ሞሮኮ በባህል፣ በሐይማኖት እና በሌሎች የቆየ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በቀጣይ በሰላም ግንባታ እና በአብሮነት ላይ ለሚያከናውኑት ተግባራት አመች ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
አምባሳደር ነዛሃ አላኦኢ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ችግር የምታልፍበት መንገድ እና ፈተናን የመቋቋም አቅሟን እንደሚያደንቁ ገልፀዋል።
ሞሮኮ ከዚህ የምትማረው ነገር እንዳለ ጠቅሰው፤ በቀጣይ በሰላም ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የሀገራቱን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል የሞሮኮ ንጉስ መሀመድ አምስተኛ ፋውንዴሽን በአዲስ አዲስ አበባ እንደሚከፈትም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሞሮኮ የጋራ ኮሚሽን ለመመስረት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም አምባሳደሯ መግለጻቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡