አምባሳደር ታዬ ከደቡብ አፍሪካና ቻይና ሚኒስትሮች ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ከደቡብ አፍሪካና ቻይና ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ በሩሲያ እየተካሄደ ከሚገኘው የብሪክስ ስብሰባ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ ከቻይና አቻቸው ዋንግ ይ ጋር ባደረጉት ውይይትም ፥ በተለያዩ የትብብር መስኮች የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል ነው የተባለው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሰደር ታዬ ከደቡብ አፍሪካ የአለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋርም በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም የሀገራቱን የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡