እስካሁን 2 ነጥብ 6 ቢሊየን የቡና ችግኝ ማዘጋጀት ችለናል-አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ አመት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኝ ለማዘጋጀት አቅደን እስካሁን ባለው አፈፃፀም ከእቅድ በላይ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ለማዘጋጀት ችለናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ÷”የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ በ2011 ዓ.ም፣ በ“ነቀምቴ አዋጅ” ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ለሀገራችን ብሎም ለክልላችን እያስገኘ ካለው ውጤት በተጓዳኝ አርሶ አደራችንንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው”ብለዋል።
ኢኒሼቲቩ በ2011 ዓ.ም 997 ሚሊየን የቡና ችግኝ በመትከል የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው በ2015 ዓ.ም 1ነጥብ 33 ቢሊየን የቡና ችግኝ ለመትከል ችለናል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ በአምስቱ ዓመታት ሂደት ከ866 ሚሊየን ሄክታር በሚልቅ አዲስ መሬት ላይ፣ ከ5 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ቡና መተከሉን ገልፀዋል፡፡
በተደረገ ርብርብ በ2011 ዓ.ም 2 ሚሊየን ሄክታር ላይ የነበረው የክልሉ የቡና ሽፋን በ2015 ዓ.ም ወደ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር ማደጉንም አመላክተዋል፡፡
በተመሳሳይ በ2011 ዓ.ም 966 ሺህ ሄክታር ላይ የነበረው የምርት ሰጪ ቡና ሽፋን በ2015 ዓ.ም ወደ 1 ነጥብ 31 ሚሊየን ሄክታር ከፍ አድርገናል፤ እዚህም ላይ በሁለቱም (በተከላውና ምርት ሰጪ ቡና ሽፋን በማሳደግ) ረገድ የአራቱ የወለጋ ዞኖች ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
በዚህ አመት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኝ ለማዘጋጀት አቅደን እስካሁን ባለው አፈፃፀም ከእቅድ በላይ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ለማዘጋጀት ችለናል ነው ያሉት።
ከዚህ አፈፃፀም ወደ ግማሽ የሚጠጋው (1 ነጥብ 13 ቢሊየን) የአራቱ የወለጋ ዞኖች ድርሻ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም በ2016 ዓ.ም የምርት ዘመን ምርት የሚሰጥ የቡና ሽፋን 1 ነጥብ 45 ሚሊየን ሄክታር ለማድረስ አቅደን እየተንቀሳቀሰን ነው ብለዋል፡፡