ፕሬዚዳንት ፑቲን ሀገራቸው ኒውክሌር ለመጠቀም የሚያስችል የሉዓላዊነት ስጋት እንደሌለባት አስታወቁ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአሁኑ ወቅት ሀገራቸው ኒውክሌር ለመጠቀም የሚያስችል የሉዓላዊነት ስጋት እንደሌለባት አስታወቁ።
ሩሲያ ኒውክሌር ለመጠቀም የሚያስገድዳት ወቅታዊ ስጋት ባይኖርም አንዳንድ የምዕራባውያንን ዒላማ ለመምታት ለሌሎች ሀገራት የጦር መሳሪያዎችን ልትልክ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀም የሚቻለው ልዩ በሆኑ ጉዳዮች ብቻ ነው ሲሉ በሴንት ፒተርስበርግ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ የገለጹት ፑቲን÷ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ጉዳይ ተፈጥሯል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
ዩክሬን በሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን በጦር መሣሪያዎቻቸው እንድትመታ ለፈቀዱ አንዳንድ የኔቶ አጋሮች ምላሽ ለመስጠትም ሞስኮ የምዕራብ ሀገራት ተቃዋሚዎችን የማስታጠቅ መብቷ የተጠበቀ ነው ሲሉ ከቀናት በፊት የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ደግመዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ፑቲን አብዛኛው የጦር መሳሪያ ወዴት ሊላክ እንደሚችል ከማብራራት ተቆጥበዋል፡፡
አክለውም በውጊያ ቀጠና የጦር መሳሪያ እየቀረበና በሉዓላዊ ግዛታችን ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ እየተሰጠ ባለበት ወቅት እኛም በተመሳሳይ እንዳናደርግ ለምን መብት አይኖረንም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ነገር ግን ይህንን ከሚቀጥለው ቀን ጀምሮ ለማድረግ ተዘጋጅተናል እያልኩ አይደለም፤ እንዲህ ያለው ነገር የዓለምን መረጋጋት ያናጋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
አሜሪካ እና ጀርመን በቅርቡ ለኪየቭ በሚያቀርቡት የረዥም ርቀት ተወንጫፊ የጦር መሳሪያ በሩሲያ አንዳንድ ኢላማዎችን እንድትመታ ፍቃድ መስጠታቸውን ዘ ዋሽንግተን ታይምስ በዘገባው አስታውሷል።